የመምሪያ አስተባባሪዎች
መጋቢ ንጉሴ ወርቁ
የወንጌል ስርጭትና ሐዋሪያዊ ተልዕኮ መምሪያ አስተባባሪ
መጋቢ ንጉሤ ወርቁ አሰላ በምትባል የአርሲ ዋና ከተማ ውስጥ ጌታን አገኝተው ወደ አገልግሎት በመምጣት፤ ከ 15 አመት በላይ የአሰላን አማኑኤል በመጋቢነት ሲያገለግሉ ቆይተዋል፡፡ ከዚሁም በላይ መጋቢ ንጉሤ በማስተማር እና በስበከት አገልግሎታቸው ወደ ተለያየ ቦታ እየተዘዋወሩ አብያተ ክርስቲያናትን አገልግለዋል፡፡ በአሁኑ ሰዓትም በኢትዮጵያ አማኑኤል ኅብረት ቤ/ክ ዋና ጽ/ቤት የወንጌል ስርጭት እና ሐዋርያዊ ተልዕኮ መምሪያን በማስተባበር ላይ የሚገኙ ሲሆን፤ የትምህርት ዝግጅታቸውም በስነ መለኮት የመጀመሪያ ዲግሪ፣ የሁለተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ በሊድ ስታር ዩኒቨርስቲ በክርስቲያናዊ አመራር እየሠሩ ነው፡፡
መጋቢ ጌታሁን አበበ
የእረኝነት መምሪያ አስተባባሪ
መጋቢ ጌታሁን አበበ በናዝሬት ከእንቅስቃሴው መነሻ ጀምሮ በተለያየ ኃላፊነት ሲያገለግሉ የነበረ ሲኾን፤ ከጌታ ዘንድ በደረሳቸው ጥሪ ለአገልግሎት በመለየት በሆሳእና፣ በቦዲቲ ለቤተክርስቲያን መተከል ምክንያት ሆነዋል፡፡ በተለይም በቦዲቲ አማኑኤል ኅብረት ቤ/ክ ረዘም ላለ ጊዜ በመጋቢነት አገልግለዋል፡፡ በአሁኑ ሰዐት መጋቢ ጌታሁን በዋናው ጽ/ቤት የእረኝነት መምሪያን ያስተባብራሉ፡፡ መጋቢው በስነ መለኮት የመጀመሪያ ዲግሪ ከመሰረተ ክርስቶስ ኮሌጅ ወስደዋል፡፡ ባለትዳር እና የሦስት ልጆች አባትም ናቸው፡፡ ከጽ/ቤት ኃላፊነታቸውም ባሻገር እግዚአብሔር በሰጣቸው ጸጋ በመስበክ እና በማስተማር ያገለግላሉ፡፡
መጋቢ ስንታየሁ በቀለ
የወጣቶች፥ የሴቶችና የህፃናት አገልግሎት አስተባባሪ
መጋቢ ስንታየሁ በቀለ በሐረር በነበረው የሰንበት ትምህርት እንቅስቃሴ፣ በዛ ከነበሩ ወገኖች ጋር የእንቅስቃሴው መሪ ነበሩና የሐረር አማኑኤል ኅብረት ቤ/ክንም እንዲወለድ ምክንያት ከነበሩት ወገኖች መካከልም አንዱ ናቸው፡፡ ከእንቅስቃሴው መጀመሪያም ጀምሮ በመሪነት እንዲሁም በጅጅጋ እና በድሬዳዋ በጌታ ጸጋ ቤተክርስቲያን በመትከል አገልግለዋል፡፡ መጋቢ ስንታየሁ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከመሰረተ ክርስቶስ ኮሌጅ በስነ መለኮት የወሰዱ ሲሆን፤ የፍቅር ተሐድሶ የተሰኘ አንድ መጽሐፍም ጽፈዋል፡፡ እግዚአብሔር በሰጣቸው ጸጋም በመስበክ እና በማስተማር በተለያዩ ቦታዎች ያገለግላሉ፡፡ ከ 2010 ዓ.ም ጀምሮም ወደ ኢትዮጵያ አማኑኤል ኅብረት ቤ/ክ ዋና ጽ/ቤት በመምጣት የወጣቶች፣ ሴቶች እና ሕፃናት አገልግሎትን በማስተባበር ያገለግላሉ፡፡
መጋቢ ይድነቃቸው አውግቸው
የትምህርትና ስልጠና መምሪያ አስተባባሪ
በናዝሬት በነበረው የሰንበት ትምህርት ቤት እንቅስቃሴ ከመስራቾች አንዱ ናቸው፡፡ በአማኑኤል ኅብረት ቤተክርስቲያን በትምህርት ዝግጅት ክፍል ኃላፊነት ተመድበው የተለያዩ ትምህርቶችን በማዘጋጀትና ስነመለኮት በማስተማር፣ እንዲሁም በናዝሬት አጥቢያ በሽምግልና ለአምስት ዓመታት ያክል አገልግለዋል፡፡ እግዚአብሔር በሰጣቸው የማስተማር ጸጋም የተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት የሚያገለግሉ ሲሆን፤ ከቅድስት ሥላሴ እና ከኢትዮጵያ ሙሉ ወንጌል ሥነ መለኮት ኮሌጆች ሁለት ዲግሪ ሠርተዋል፡፡ በአሁን ወቅትም በኢትዮጵያ አማኑኤል ኅብረት ቤተክርስቲያን ዋና ጽ/ቤት የትምህርትና ስልጠና መምሪያን አስተባባሪ ሆነው በማገልገል ላይ ይገኛሉ፡፡