የእምነት መግለጫ
የኢትዮጵያ አማኑኤል ኅብረት ቤተ ክርስቲያን የእምነት መግለጫ በሚከተሉት አስተምህሮአዊ እውነቶች ላይ የተመሠረተ ነው፡፡
- መጽሐፍ ቅዱስ፡
መጽሐፍ ቅዱስ በእስትንፋሰ-እግዚአብሔር አማካይነት በመንፈስ ቅዱስ በተነዱ ቅዱሳን የእግዚአብሔር ሰዎች የተጻፈ የእግዚአብሔር ቃል ሲኾን፥ በሚያረጋግጠው ኹሉ ስሕተት የማይገኝበት፥ እውነተኛ፥ ተአማኒና በቂ፥ እንዲሁም ሥልጣናዊ መጽሐፍ መኾኑን እናምናለን። ስለዚህ የመጨረሻ የእውነት መለኪያ እንደ መኾኑ መጠን በእምነታችን፥ በምግባራችንና ልምምዳችን ኹሉ ላይ ላዕላይ መለኪያና የመጨረሻ ዳኛ መኾኑን እናጸናለን። እንዲሁም ለሰዎች ልጆች ሕይወት መጽናናትን፥ ምሪትን፥ ጽድቅን፥ በቅድስና ለመኖርም ድጋፍንና ምክርን የሚሰጥ ብቸኛ መጽሐፍ መኾኑን እናምናለን።ዘጸ.20፥1፤ 34፥1፡ 15-17፡ 27፤ 31፥18፤ 2ሳሙ. 23፥2፤ 1ዜና. 28፥19፤ ኤር. 36፥1-4፤ ሉቃ. 9፥35፤ ዮሐ. 17፥8፤ 2ጢሞ. 3፥16-17፤ ዕብ. 1፥1-4፤ 1ጴጥ. 1፥28፤ 2ጴጥ. 1፥3፡ 21፤ ራእ. 1፥17-19። - ሥሉስ አሐዱ አምላክ፡
የከበረ ዓላማ ባለውና ራሱን በሦስትነት በገለጠ በአንድ እውነተኛ ሕያው አምላክ እግዚአብሔር አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ እናምናለን። እግዚአብሔር አሐዱ-ሥሉስ አምላክ ነው። እርሱም በሦስት አካላት፥ ነገር ግን በማይከፋፈል አንድ ህላዌ፥ ማንነት፥ መለኮት፥ አንዋዋር፥ አገዛዝ፥ ፈቃድና ሥልጣን ለዘላለም የነበረ፥ ያለና የሚኖር እውነተኛ ሕያው አምላክ ነው። እርሱ ቅዱስ፥ ፍጹም፥ የማይለወጥ ከኻሌ ኩሉ፥ ከሣቴ ኩሉ፥ አዕማሬ ኩሉ፥ የማይወሰን፥ የፍጥረት ኹሉ መሠረት እና በመግቦቱም የፍጥረቱ ጠባቂ ነው። ዘላለማዊው አምላክ እግዚአብሔር አብ፥ ወልድ፥ መንፈስ ቅዱስ የመላለሙ ጌታና ገዢ ኾኖ ይኖራል። የሚታየውንና የማይታየውን ኹሉ እንደፈቃዱ ምክር ያስተዳድራል። በዘላለማዊ ዕቅዱ መላለሙን በፈጣሪነቱ ያስገኘ ሉዓላዊው አምላክ ከፍጥረቱ የተለየ ምጡቅ ሲኾን፥ በገዛ ዓለሙ ውስጥ እንደ ፈቃዱ ጣልቃ ይገባል። በምእመናኑም መካከል ያድራል። (ዘፍ. 1፥1-28፤ 11፥7፤ ዘዳ. 6፥4-5፤ መዝ. 139፥7-12፤ ኢሳ. 40፥28፤ ማቴ. 28፥19፤ ሉቃ. 3፥21-22፤ ዮሐ.1፥1-3፤ 14፥16፤ 17፥11፤ የሐዋ. 14፥15፤ 17፥24-29፤ ኤፌ. 1፥11፤ ቈላ.1፥15-17፤ ኢሳ. 44፥6-8፤ 45፥5፤ ማቴ. 3፥16-17፤ 28፥19-20፤ ዮሐ.14፥16፤ 2ቆሮ. 13፥14፤ ኤፌ. 4፥6). - እግዚአብሔር አብ፡
እግዚአብሔር አብ፥ በማንኛውም መንገድ የማይወሰንና ሊወሰንም የማይችል ኹሉን ቻይ ዘላለማዊ፥ የማይለወጥ፥ የኹሉ ፈጣሪ፥ ኹሉን የሚያውቅ፥ በጥበብ የላቀ፥ ኹሉን የሚወድ፥ ፍጹም ቅዱስ ሉዓላዊ ገዢና ፍጥረት ዓለምን በእጁ የያዘ መኾኑን እናምናለን። እግዚአብሔር አብ የጌታችን የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የባሕርይ አባት እንዲሁም የእውነተኛ አማኞች ኹሉ የጸጋ አባት ነው፡፡ ዘፍ. 3፥16፤ 22፥15-18፤ ዘጸ. 33፥20፤ ዘኍ. 23፥19፤ ኢሳ. 40፥12፤ 45፥18-19፤ ዮሐ. 1፥18፤ 3፥16፤ የሐዋ. 3፥25-26፤ 1ጢሞ. 6፥16። - እግዚአብሔር ወልድ፡
እግዚአብሔር ወልድ በሥጋ የተገለጠው ዘላለማዊ ቃል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፤ እርሱም፥ የእግዚአብሔር አብ ዘላለማዊ አንድያ ልጅ፥ ፍጹም ሰውና ፍጹም አምላክ መኾኑን እናምናለን። ጌታችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመለኮታዊ ተአምር በኀይለ መንፈስ ቅዱስ ከድንግል ማርያም በሥጋ ተጸንሶ የተወለደ፥ በሙአለ ሥጋዌው ያለ ምንም ኀጢአት የተመላለሰ፥ በጴንጤናዊው በጲላጦስ ዘመን ስለ ኀጢአታችን መከራ የተቀበለ፥ ፍጹምና በቂ የማስተሰረያ መሥዋዕት በመኾን ይቤዠን ዘንድ በእኛ ምትክ የተሰቀለ፥ የተቀበረ፥ በኀይልና በክብር በሦስተኛው ቀን ከሙታን የተነሣ፥ ከትንሣኤው በኋላ ለብዙዎች ታይቶ በከበረው አካሉ ወደ ሰማይ ያረገ፥ በአባቱ ቀኝ ተቀምጦ ለምእመናን የሚማልድና የእግዚአብሔርን የዘላለም ዕቅድ ለመጠቅለልና በሕያዋንና በሙታን ላይ ይፈርድ ዘንድ በታላቅ ክብርና ኀይል ዳግም እንደሚመለስ እናምናለን። ማቴ.1፥18፡ 20-25፤ 2፥12፤ ሉቃ. 1፥30-39፤ 2፥4-7፤ 1ጢሞ. 2፥5-6፤ ዮሐ. 1፥1-4፡ 14-18፤ 17፥5፤ 1ዮሐ. 5፥20፤ ፊልጵ. 2፥6-8፤ ቈላ. 1፥15-20፤ 3፥1፤ ዕብ.1፥1-3፤ 2፥9፤ 1ዮሐ. 2፥2፤ 1ቆሮ. 15፥3-4፤ ሉቃ. 24፥-43፤ ሐዋ. 2፥24፤ 1ጴጥ. 1፥21፤ ማቴ. 25፥31-46፤ ማቴ. 16፥27፤ ዮሐ. 14፥3፤ 1ተሰ. 4፥13-18፤ ራእ.22፥12-20። - እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ፡
እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ የሥላሴ ሦስተኛው አካል ኾኖ ከአብና ከወልድ ጋር የተካከለ የባሕርይ አምላክ መኾኑን እናምናለን። መንፈስ ቅዱስ ምእመናንን የሚያስተምር፥ የሚመራ የሚያጽናና፥ ልዩ ልዩ መንፈሳዊ የጸጋ ስጦታዎችን እንደ ፈቃዱ እያደላቸው የክርስቶስን አካል እንደሚያንጽ፥ የቅድስና ሕይወት እንዲኖሩ እንደሚያስችላቸው፥ ለአገልግሎት ኀይልን እንደሚያስታጥቃቸው፥ ስለ ቅዱሳን እንደሚማልድ፥ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሚመሰክር፥ ዓለምን ስለ ኀጢአት፥ ስለ ጽድቅና ፍርድ እንደሚወቅስ፥ ምእመናን ኹሉ ወደ ክርስቶስ አካል ያጠመቃቸው እንሱ እንደ ኾነ እና በእነርሱ ውስጥ በማደር ለቅዱስ ሕይወትና ለፍሬያማ አገልግሎት ዘወትር እንደሚሞላቸው እናምናለን። ዘፍ. 1፥2፤ ኢዮ. 33፥4፤ መዝ. 139፥7፤ ኢሳ. 11፥2፤ ማቴ. 28፥19-20፤ ዮሐ. 14፥26፤ 15፥26፤ 16፥8-11፤ የሐዋ. 1፥8፤ 2፥1-4፤ 5፥28-32፤ ሮሜ. 8፥26፤ 1 ቆሮ. 2፥9-10፤ 12፥4-13፤ ዕብ.9፥14። - የሰው አፈጣጠርና በኀጢአት መውደቅ፡
የሰው ዘር፥ ወንድና ሴት ኾኖ፥ በእግዚአብሔር መልክ የተፈጠረ በፍጥረትም ኹሉ ላይ የገዢነት ሥልጣን የተሰጠው ክቡር ፍጥረት መኾኑን እናምናለን። የእግዚአብሔርን ትእዛዝ በመተላለፍ በውድቀት ኀጢአት ምክንያት ከእግዚአብሔር በመለየት የሞት ተገዢ መኾኑን በማንኛውም መንገድ ራሱን ከውድቀት ማዳን እንደማይቻለው እናምናለን። በሰው መተላለፍ ምክንያት ኀጢአት ወደ ዓለም መግባቱን መላው ዓለም ከእርግማን በታች መውደቁን እናምናለን። ዘፍ. 1፥26-28፤ 2፥16-17፥ 3፥1-7፡ 16-19፤ የሐዋ 4፥12፤ ሮሜ. 3፥25፤ 5፥12-21፤ 6፥23፤ 1ቆሮ. 15፥21-22፤ ኤፌ. 2፥1-9። - ድኅነት፡
ኀጢአተኛው የሰው ልጅ ከእግዚአብሔር ጋር ሊታረቅ የሚችለው በእግዚአብሔር ጸጋ አማካይነት በክርስቶስ ኢየሱስ በማመን ብቻ መኾኑን እናጸናለን። ሰው በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ በመታመን ስለ ኀጢአቱ ንስሐ ሲገባ በዐዲስ ልደት መታጠብና በመንፈስ መታደስ ዳግመኛ ተወልዶ የእግዚአብሔር ልጅነትን ጸጋ እንደሚቀበል፥ በእግዚአብሔር ጸጋ ምክንያት ጻድቅ ኾኖ እንደሚቈጠር፥ በመንፈስ ቅዱስ ኀይል አማካይነት በቅድስና ሕይወት ለመመላለስ እንደሚችል፥ የዘላለም ሕይወት እንደሚኖረው እንጂ እንደማይጠፋ እናምናለን። ሉቃ. 13፥3, 5፤ ዮሐ. 1፥12፤ 3፥3-5፤ 10፥27-28፤ የሐዋ. 3፥19-20፤ 13፥38-39፤ 20፥21፤ ሮሜ. 3፥24፤ 5፥1፤ ኤፌ. 2፥8-9፤ ቲቶ 3፥4-5፤ 1ጴጥ.1፥15-16፤ 1ዮሐ. 5፥13፤ ገላ. 5፥16-25፤ ኤፌ. 5፥18። - የቅዱሳን አንድነት፡
ኩላዊትና መላለማዊ ኾና በምትገኘው የክርስቶስ አካል ውስጥ በሚገኙ፥ በመንፈስ ቅዱስ ኀይል ዳግመኛ በተወለዱ ሰዎች ታንጻ በተጨባጭ ኹነት ደግሞ በቤተ ክርስቲያንነት ተገልጣ በምትታየው የምእመናን አንድነት እናምናለን። ቤተ ክርስቲያን ቅድስትና መላለማዊ ኾና በእርስዋም ውስጥ በዘመናት ኹሉ የነበሩና ያሉ እውነተኛ አማኞች በሙሉ በአባልነት የሚገኙባት የክርስቶስ አካል መኾኗን፥ በእምነት እናጸናለን። በምድራዊና አጥቢያዊ መገለጫዋ ደግሞ በወንጌል ቃል ኪዳንና ኅብረት በጋራ በመተባበር፥ የጥምቀትና የጌታ ራት ሥርዐትን በመፈጸም፥ ለጋራ መተናነጽና መጽናናት እንዲሁም ወንጌልን በመላው ዓለም ለማወጅ ሲባል በቅዱስ ቃሉና በመንፈስ ቅዱስ የጸጋ ስጦታዎች በማገልገልና እግዚአብሔር በጠራቸው አገልጋዮች በመመራት በጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ባሉ አማኞች የተገነባች ማኅበረ ምእመናን ናት። ስለኾነም፥ በአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ሕይወት ውስጥ መካተትና በትጋት መሳተፍ የእያንዳንዱ አማኝ መብትና ኀላፊነት ነው። ማቴ. 28፥20፤ የሐዋ. 2፥41፡ 47፤ 6፥1-7፤ 11፥21-23፤ 20፥7፤ 1ቆሮ. 1፥1-13፤ 4፥17፤ 12፥20-28፤ 14፥23፤ 2ቆሮ. 8፥1-5፤ ገላ. 6፥2፤ 1ጢሞ. 3፥1-9፤ 4፥13፤ 2ጢሞ. 3፥16-4፥2፤ ቲቶ 1፥6-9፤ 3ዮሐ. 9፤ ቈላ. 1፥18፤ ኤፌ. 1፥22-23፤ 4፥11-16፤ 1ተሰ. 4፥13-18፤ ዕብ. 10፥23-25፤ ። - የክርስቶስ ዳግም ምጽአት፥ የሙታን ትንሣኤና ፍርድ፡
ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ተነሥቶ ወደ ሰማይ ሲያርግ እንደ ታየው እንዲሁ በአካልና በሚታይ ኹኔታ በታላቅ ኀይልና ክብር ተመልሶ እንደሚመጣ እናምናለን። በዳግመኛ ምጽአቱም የሙታን ትንሣኤ እንደሚፈጸም፥ ጻድቃን ለዘላለም ክብር በትንሣኤ አካል ተነሥተው የዘላለም ሕይወት እንደሚቀዳጁ፧ ኀጥአንም ለዘላለም ሞትና ጥፋት እንደሚነሡ፥ በሕያዋንና በሙታንም ኹሉ ላይ የመጨረሻው ፍርድ እንደሚሰጥና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከቅዱሳኑ ጋር እንደሚነግሥ እናምናለን። ማቴ. 25፥46፤ 16፥27፤ ዮሐ. 14፥2-3፤ የሐዋ. 1፥11፤ 1ተሰ. 4፥16፤ 1ቆሮ. 15፥12-58፤ ራእ. 20፥12. - መላእክት፡
ቅዱሳን መላእክት ሕያው እግዚአብሔርን ለማገልገል የተፈጠሩ መንፈሳውያን አገልጋዮች መኾናቸውን እናምናለን። በብሉያትም ኾነ በሐዲሳት እኒህ መላእክት እግዚአብሔርን በመታዘዝ ቅዱሳንን ለማገልገል ይላካሉ። ቅዱሳን መላእክት አምልኮ አይቀበሉም። አምልኮና ስግደት የተገባው እግዚአብሔር ብቻ መኾኑን እናምናለን። ዘፍ. 16፥7፡ 21፥17፤ መሣ. 6፥1፤ 2ሳሙ. 24፥16፤ መዝ. 91፥11፤ ኢሳ. 6፥1-3፤ ዘካ. 1፥12፤ ሉቃ.1፥19፤ የሐዋ. 8፥26, 29፤ ራእ. 5፥11፤ 22፥8-9. - ሰይጣንና መናፍስተ ርኩሳን፡
ሰይጣን መንፈሳዊ አካል ያለውና በትዕቢት ተነሣሥቶ በማመፁ ምክንያት በእግዚአብሔር የተጣለ መልአክ ነው። ሰዎችንና ዓለሙን በክፋት የሚመራ፥ የማያምኑትን ሰዎችና የክፉ መናፍስትን ሐሳብ በማሳወር ለጥፋት የሚነዳ የክፋት ኹሉ ምንጭና የወደቁ መላእክት መሪ ነው። ሰይጣን የእግዚአብሔርና የሰው ልጆች ኹሉ ጠላት ሲኾን በኀጢአትና ክፋት የተበላሸ የዚህ ዓለም ሥርዐት አምላክ፥ የሐሰትም አባትና የአማኞች ከሳሽ ነው፤ በዘመኑ መጨረሻ በእግዚአብሔር ጻድቅ ፍርድ ምክንያት ወደ ተዘጋጀለት የፍርድ እሳት ከመላእክቱ ጋር እንደሚጣል እናምናለን። አጋንንት ከሰይጣን ጋር የወደቁ፥ ከሰይጣን ጋር በመኾንም የእግዚአብሔርን ሥራ የሚቃወሙ እና በመጨረሻውም ከሰይጣን ጋር የሚፈረድባቸው የወደቁ መላእክት ናቸው። ዘፍ. 3፥1-6፤ ኢሳ. 14፥12-17፤ ሕዝ. 28፥13-18፤ ማቴ. 10፥24፤ 12፥24፤ 25፥41፤ ሉቃ.8፥31፤ ዮሐ. 8፥44፤ 14፥16፥ 2ቆሮ. 4፥4፤ መሳ. 6፤ ራእ. 12፥10፤ 20፥10።