የእረኝነት መምሪያ

የእረኝነት አገልግሎት መምሪያችን የአጥቢያዎቻችንንና የመጋቢዎቻችንን ሕይወትና አገልግሎት በመከታተል፤ በማሰልጠንና እንዲሁም ምደባና ክትትል በማድረግ ከፍተኛ ሥራ እየሠራ ይገኛል። በሥሩም የጋብቻና ቤተሰብ ክፍልና የልጆችና የወጣቶች አገልግሎት ዘርፍ በመክፈት አጥቢያዎቻችን በብዙ አየደገፈና እየጠቀመ ይገኛል፡፡ በመላው አገሪቱም በቤተ እምነቷ እውቅና ያገኙ 350 መጋቢዎች ሲኖሩ፤ 2720 የሚሆኑ የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ደግሞ በቤተ እምነቷ ይገኛሉ፡፡

የኢትዮጵያ አማኑኤል ኀብረት ቤተክርስቲያን የምትከተለው የመጋቢያን አመራር እንደመሆኑ አጥቢያዎች በጠንካራ መጋቢያን እንዲመሩ ከፍተኛ ጥረት ታደርጋለች፡፡ በባለፉት 10 ዓመታት ብቻ እንኳ ከ100 የሚበልጡ መጋቢዎችን በተለያዩ ከተሞች መሾም የቻለች ሲሆን በተመሳሳይ ሁሉም አጥቢያዎች የራሳቸው መጋቢ እብዲኖራቸው እየሠራች ትገኛለች፡፡ ቤተክርስቲያኒቱ የመጋቢዎችን አጠቃላይ የአመራር ብቃት የምታጎለብትበት የተለያዩ አጫጭር ስልጠናዎችን በማዘጋጀት ብቁ መጋቢያዊ አገልግሎት እንዲሰጥ ታግዛለች፡፡

በተጨማሪም በዋናው ጽ/ቤት ደረጃ የእረኝነት መምሪያን የሚያስተባብር አካል ከማስቀመጥ ባለፈ በቅርብ እርቀት የአጥቢያዎችን አጠቃላይ ደኅንነት የሚከታተሉ የክልል እና የዞን ቢሮዎችን አቋቁማለች፡፡ ምንም እንኳ ከአቅም ማነስ ጋር ተያይዞ በሁሉም አካባቢዎች የዞን ቢሮዎችን መክፈት ባትችልም አሁን ባሉት የዞን እና የክልል ቢሮዎች በተቻለ መጠን ሁሉም አጥቢያዎች በሚፈለገው መጠን አስፈላውን አገልግሎት እንዲያገኙ እየሠራች ትገኛለች፡፡ ከዚህ ጋር ለቤተሰብ አገልግሎት ትኩረት በመሰጠት እና በክፍል ደረጃ ቢሮን በማቋቋም እና ለቦታው ሸክም ያለውን ሰው በመመደብ አረአያነት ያለው ሥራ እየሠራች ትገኛለች፡፡

ደቀመዛሙትን ማፍራት፣ አገልጋይነትንና መሪነትን ማጎልበት

የኢትዮጵያ አማኑኤል ኀብረት ቤተክርስቲያን አጥቢያዎችን ከመትከል እና አዳዲስ ነፍሳትን ለክርስቶስ ከመማረክ ጎን ለጎን አማኞች በሕይወታቸው ጠንክረው እና እውነተኛ የክርስቶስ ደቀመዛሙርት ሆነው እንዲኖሩ ጠንክራ ትሠራለች፡፡ በሂደትም የማያሳፍሩ የእግዚአብሔ መንግሥት አገልጋዮች እና መሪዎች ይወጡ ዘመን ተከታታይነት ባለው መልኩ መሰረታዊ ትምህርቶችን በማዘጋጀት እና በማሰራጨት እንዲሁም በተለያዩ ጊዜያት ልዩ ልዩ ስልጠናዎችን በማዘጋጀት አገልጋዮችን የማብቃ ሥራ ስትሠራ ቆይታለች፡፡

በተንቀሳቃሽ መልኩ በተለያዩ ክልሎች በከፈተቻቸው የስነ መለኮት እና የአመራር ጥበብ ማስተማሪያ ትምህርት ቤቶች አማካይነትም ከ1999 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 2006 ዓ.ም ድረስ ከ750 በላይ መሪዎችን በዲፕሎማ ደረጃ አሰልጥና ስታስመርቅ በአሁን ሰዓትም ከ500 በላይ የሚሆኑ አገልጋዮች በሁለቱም መርኃ ግብር ስልጠና እያገኙ ይገኛሉ፡፡ በተጨማሪም በአገር ውስጥ በተለያዩ የስነ መለኮት ትምህርት ቤቶች ገብተው በዲግሪው መርኃ ግብር ትምህርታቸውን መከታተል የቻሉ ከ50 በላይ መሪ አገልጋዮች ያፈራች ሲሆን፤ በቁጥር ጥቂት ቢሆኑም በሀገር ውስጥ እና ከሀገር ውጪ በማስተርስ ዲግሪ ደረጃ አገልጋዮች የትምህርት እድል እንዲያገኙ ተንቀሳቅሳለች፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለም የበለጠ በቋሚነት የሰለጠኑ መሪ አገልጋዮችን ለማፍራት ይቻላት ዘንድ፣ በድግሪ መርሃ ግብር የስነ መለኮት ትምህርት ቤት ከ2008 ዓ.ም ጀምራ ውጤታማ ሊባል በሚችል ሁኔታ የመጀመሪያ ዙር አስመርቃለች፡፡

የአገልግሎት ዘርፍ ማስተባበሪያዎች