መጋቢ ጌታሁን ታደሰ

የቤተ ክርስቲያኒቱ ፕሬዝደንት እና ሥራ አስፈፃሚ መሪ

መጋቢ ጌታሁን ታደሰ ከኢትዮጵያ አማኑኤል ኀብረት ቤተክርስቲያን የምስረታ ታሪክ ጀምሮ ላለፉት 30 አመታት በቤተክርስቲያኒቱ ውስጥ ያገለገሉ ሲሆን በተለይ በ1980ቹ አጋማሽ በብዙ ከተሞች በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የወንጌል የተሐድሶ ንቅናቄ ሲጀመር ወለንጭቲ በምትባል ከተማ /ከናዝሬት 25 ኪ.ሜ/ “ደብረ ሠላም ቅዱስ ጊዮርጊስ ደብር” ውስጥ የተጀመረውን የሰንበት ት/ቤት ከሌሎች ወንድሞች እና እህቶች ጋር በመምራት እና በማስተባበር ትልቅ አስተዋፅኦ አበርክተዋል፡፡ በኃላም የወንጌል የተሀድሶው ንቅናቄ እየተቀጣጠለ ሲመጣ የደብሩ አለቆች በተቃውሞ መሀበሩን ከቅጥር ግቢው እንዲለቅ ሲያስገድዱት መጋቢው መሀበሩን በመምራት፣ በማደራጀት እና የእግዚአብሔርን ወንጌል በፅናት በመስበክ አገልግሏል፤ በተለይ በአጥቢያዋ ላይ በ1987 ዓ.ም ከፍተኛ የሆነ ስደት፣ ተቃውሞ እና የንብረት ማውደም መከሰቱን ተከትሎ ቤተክርስቲያኒቱ በከፍተኛ ጫና ውስጥ በወደቀችበት ጊዜ በፅናት ከቆሙ ወንድሞች ጋር በመሆን ያደረጉት ተጋድሎ በቤተክርስኒቱ ታሪክ የማይረሳ እውነት ነው፡፡

መጋቢ ጌታሁን ታደሰ በአገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረው የተሐድሶ ንቅናቄ ተቋማዊ ቅርጽ እየያዘ እና በጊዜው በናዝሬት የተጀመረው ሰፊ የተሐድሶ ንቅናቄ አገራዊ ስራውን ማስተባበር ሲጀምር መጋቢው ወደ ተለያዩ ከተሞች በመላክ አጥቢያዎችን የመምራት እና የእግዚአብሔርን ቃል በስፋት የማስተማር ስራ በስፋት አከናውኗል በኃላም በአዲስ አበባ የምትገኘውን የመርካቶ ሠባተኛ አማኑኤል ኀብረት ቤተክርስቲያን አጥቢያን በዋና መጋቢነት ከመምራት ጎን ለጎን በዋናው ጽ/ቤት የእረኝነት መምሪያውን በማስተባበር ለ6 አመታት ካገለገሉ በኃላ – በ2005 ዓ.ም መስከረም ወር በተደረገ ጠቅላላ ጉባኤ የኢትዮጵያ አማኑኤል ኀብረት ቤተክርስቲያንን በፕሬዝዳንትነት እንዲመሩ ከተመረጡ ጊዜ ጀምሮ በትጋት እና በሀላፊነት ስሜት ስራቸውን በማከናወን ላይ ይገኛሉ፡፡

መጋቢ ጌታሁን ታደሠ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከመሠረተ ክርስቶስ ኮሌጅ በቴዎሎጂ የተቀበሉ ሲሆን ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ በአመራር ጥበብ ናይሮቢ ኬኒያ ከሚገኘው በፓን አፍሪካ ክርስቲያን ዮኒቨርስቲ ተከታትለዋል፡፡ መጋቢ ጌታሁን ከሠላማዊት አድማሱ ጋር ትዳር መስርተው ላለፉት 15 ዓመታት የኖሩ ሲሆን ሁለት ወንድ እና አንዲት ሴት ልጅ አፍርተዋል፡፡

የቤተ ክርስቲያኒቱ መሪዎች